በመዲናዋ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ይሰጣል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚሰጥ የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክትባት ዘመቻው ከግንቦት 6 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
የጤና ቢሮው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለፀው፤ በክትባት ዘመቻው ዕድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 ዓመት የሆኑ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ህፃናት ይከተባሉ።
ከ3 ሺህ 400 በላይ ባለሙያዎች በክትባት ዘመቻው ይሳተፋሉ ብሏል፡፡
በክትባት ዘመቻው የኩፍኝ ክትባትን ጨምሮ ሌሎች የቫይታሚን ኤ ጠብታ እና የአንጀት ትላትል መድሃኒት ይሰጣል ተብሏል፡፡
በሲፈን መኮንን