Fana: At a Speed of Life!

“ዓድዋ ‎የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የወል ትውስታ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

“ዓድዋ ‎የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የወል ትውስታ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “‎ዓድዋ ‎የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድልና የወል ትውስታ” የተሰኘ መጽሐፍ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ‎ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ አርበኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ‎በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በመጽሐፉ ‎ላይ የዓድዋ ድል የተጋድሏችን ብርታት፣ የአባቶቻችን ጽናትና ሌሎች የተረኩበት እውነታ ተመልክቻለሁ ብለዋል።

በመጽሐፉ ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ‎የምናውቃቸውንም ይሁን ታሪክ የዘነጋቸውን ለማስታወስ ጥረት ተደርጓል ሲሉም ገልጸዋል።

ዋጋ የከፈሉትን ፋኖስ እንድናደርጋቸው የሚያግዝ ነው፤ ‎ትናንትንና ዛሬን ያገናኛል በማለት ገልጸው÷ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንንም በደንብ በመግለጽ ዓድዋን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳው ማድረግም ሌላው የመጽሐፉ አስተዋጽዖ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው እንዳሉት÷ ዓድዋ የማይታሰበውን አሳክተው የማይቻለውን ችለው የሀገርን ክብር በተግባር ያሳዩን አባቶች ታሪክ ነው።

‎እኛ ኢትዮጵያውያን ሊዘከሩ የሚገቡና በወጉ ያልተሰነዱ ታሪኮች ባለቤት ነን ያሉት ከንቲባዋ÷ ከብዙ ድካም በኋላ ይህ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል ብለዋል።

‎ዛሬ ላይ ቆመን ትናንትናችንን አውቀን የነገዋን የተሻለች ኢትዮጵያ ለመገንባት ታሪክን ማወቅ ይገባል፤ ሀገር የሚገነባው በጡብ ብቻ ሳይሆን በትውልድ አዕምሮ ውስጥ በሚቀረጽ እውቀት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የዓድዋ ጀግኖች ሀገር ለማቆየት የከፈሉትን ዋጋ ስንዘክር የእኛ ትውልድ ሕብረብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲከበር በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን የማጽናት ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

‎የእኛ ዓድዋ ፈጥኖ የሚጠናቀቅ ፕሮጀችት ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ ዓድዋዎችን የመድገም ታላቅ አደራ ተጥሎብናል ያሉት ከንቲባዋ÷ ‎እንዲህ ያሉ ታሪኮች መሰነዳቸው ለነገ ብልጽግናችን መሰረት ይጥላል ሲሉ አስረድተዋል።

በአሻግሬ ገብረወልድ (ዶ/ር) የተጻፈው መጽሐፉ ‌‎በ26 ምዕራፎች የተከፈለና ከ1 ሺህ በላይ ገጾች አሉት።

በሐይማኖት ወንድራድ‎

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.