በበልግ ወቅት የተሻለ ምርት ለማግኘት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትግራይ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በበልግ ወቅት የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበራ ከደነው፤ በበልግ ወራት 22 ሺህ ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን እና እስከ አሁን ከ8 ሺህ ሔክታር የሚልቀው መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ በበልግ ወቅት ከ400 ሺህ ሔክታር በላይ በዘር ለመሸፈን እየተሠራ ነው፡፡
እስከ አሁንም ከ60 በመቶ በላይ ያህሉ መሬት መታረሱን እና በአጠቃላይ በዘር ከሚሸፈነው መሬት ከ 59 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት አስቀድሞ ለአርሶ አደሩ መድረሱን የሥራ ኃላፊዎቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አረጋግጠዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን