የድሬዳዋ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ዕምቅ ጸጋና ታሪክ የገለጠ ነው – ከንቲባ ከድር
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ውበትና ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ያላትን ዕምቅ ጸጋና ታሪክ የገለጠ መሆኑን ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
የኮሪደር ልማት ስራው የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው፥ ምቹና ውብ ገጽታ በመፍጠር የከተማዋን ዕድገት የሚያሳልጥ የመስህብ ስፍራ እየፈጠረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተያዘው ዓመት የታቀደው የ12 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ መጠናቀቁንና በተጨማሪ የከተማዋን የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የአረንጓዴና መናፈሻ፣ የእግረኛና የባለሁለት ጎማ ተሽከርካሪ መንገድ በማዘመን ተጨማሪ ስራ ለመስራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሰው ተኮር ልማት የከተማዋን ነዋሪዎች ህይወት መቀየር የሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይ የእናቶች እንጀራ መጋገሪያ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚደረግም አንስተዋል።
“የድሬ ናፍቆት” በሚል መሪ ሃሳብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማከናወን የተገኘው ገንዘብ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በሚያሻሽሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል አመልክተዋል።
በሌላ መልኩ በአምስት ሚሊየን የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና በቴክኖሎጂ ክህሎት ልማት ዜጎችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡