Fana: At a Speed of Life!

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ስኬት በሌሎች ፋብሪካዎችም ይጠበቃል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የተገኘው የሪፎርም ውጤት በሌሎች ፋብሪካዎች እንደሚደገም ይጠበቃል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሪፎርም እንዴት እንደሚሠራ ቋሚ ዐውደ ርዕይ የሚሆን ውጤት በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ተመልክተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዛሬ 70 ዓመት በጥሩ መሠረት ላይ መገንባቱንም አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከዘመን ጋር ካልተጓዙ መቅደም ብቻውን መብለጥን አያመጣም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀድሞ የበቀለን ጆሮ በኋላ የመጣ ቀንድ ሊቀድመው ይችላል ብለዋል፡፡

እየፈጠኑና እየፈጠሩ ዘመኑን ካልቀደሙትም፤ ጊዜው ራሱ ይቀድማል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዛሬ ሦስት ዓመት ለሠራተኞቹ ደመዎዝ መክፈል ተስኖት እንደነበር አስታውሰው፤ ዕዳ እንደ መርግ ተጭኖት ነበር ብለዋል፡፡

በመሆኑም በተሠራው የሪፎርም ሥራ በቀን ያመርተው ከነበረው 1 ሺህ 500 ኩንታል ዛሬ ወደ 7 ሺህ ኩንታል አድጓል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባሻገርም ለ14 ዓመታት ከሥራ ውጭ የነበረው የብዙዎች ትዝታ ደስታ ከረሜላ እንደገና መመረት ጀምሯል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት ዘርፍም በቀን 3 ሺህ ሊትር ወትት እና 20 ሺህ ዕንቁላል ማምረት የሚችል ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ ግቢው እና መስኩ ለዓይን እንደሚማርክ አመላክተዋል፡፡

ወንጂ ዘንድሮ የፈተናውን ዘመን አልፎ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 8 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ አስገብቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ይህ ጠንካራ የሪፎርም ውጤት በሌሎቹ ፋብሪካዎች እንደሚደገም ይጠበቃል፤ ከሠራን ነገን እንቀድመዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.