Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል ዘርፉን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያሳዩ እንደሆነ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጅታል ዘርፉ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በመንግስት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነ ተገልጿል።

ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ የዲጂታል ዘርፉ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በተቀላጠፈ መንገድ ለመከወን አስችለዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)፤ በዲጂታል ሥርዓቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች በአስተዳደር እና በሌሎች ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በተለይም ደግሞ ከሙስና ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚችያስሉ ናቸው ብለዋል።

ዘርፉን ለማሳደግ በፖሊሲ እና በስትራቴጂ ከመደገፍ ባለፈ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ከሰሩ ወጣቶቻችን ከፍተኛ እመርታ ውስጥ እንዲገቡ ያስችላቸዋል በማለት ገልጸው፤ የዲጂታል ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዲጂታል ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት መመስረት፣ የዲጅታል መሳሪያዎች በሀገር ውስጥ መመረት፣ የፋይናንስ ኩባንያዎች ማደግ እና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተሰሩ ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እነዚህን ሥራዎች በዲጂታል ዘርፍ ዓለም የደርሰበት ደረጃ ላይ በአጭር ጊዜ ለመድረስ የሚያስችሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ኃይለመስቀል ጋዙ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ስርዓቶች የሰውን እና የወረቀትን ንክኪ በመቀነስ ብልሹ አሰራሮችን እንደሚያስቀሩ እንዲሁም የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪን እንደሚቀንሱ ገልጸዋል።

ወጣቶች በዲጅታል ዘርፉ በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የሥራ እድል ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉም አመልክተዋል።

የዲጅታል ፋይናንስ ዘርፉን በማሳደግ ረገድ በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየታየባቸው ሲሆን ይህም ሀገር ገቢዋን የምታሳድግበት አንዱ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጅታል መቀየር፣ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓቶችን ማስፋፋት እና ለዲጅታል ሥራዎች አጋዥ የሆኑ መተግበሪያዎች በልጽገው ወደ ተግባር እንዲገቡ መደረጋቸው ይታወቃል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.