ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት የዓለም አቀፍ ትብብርና ትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ አማካሪ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከሩሲያ 80ኛ ዓመት የድል በዓል አከባበር በተጓዳኝ ከሀገሪቷ ፕሬዚዳንት የዓለም አቀፍ ትብብርና ትራንስፖርት ዘርፍ ልዩ አማካሪና ተወካይ ኢጎር ሌቪቲን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ሩሲያ በሎጂስቲክስና በትራንስፖርት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራች የምትገኝበትን ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ትስስር ለማጠናከር ትብብር እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት፤ የረጅም ዘመን ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው በይበልጥ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗን በማንሳት፣ የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን በትኩረት እያስፋፋች እንደምትገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሩሲያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ እና አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በዚህ ረገድ የትብብር ቁርጠኝነትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢጎር ሌቪቲን በበኩላቸው፤ ተጠናክሮ የቀጠለውን የሩሲያና የኢትዮጵያ ግንኙነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለሩሲያ በአፍሪካ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር በመሆኗ ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ትብብሯን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
የሩሲያ መንግስት በኢትዮጵያ አዳዲስ የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።