Fana: At a Speed of Life!

ከ13 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች መሬት እንዲተላለፍላቸው ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 13 ነጥብ 361 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 66 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የጠየቁት መሬት ተላልፎላቸው ወደ ልማት እንዲገቡ ውሳኔ መተላለፉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኃላፊው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በዞኖች እና በልዩ ወረዳዎች በኩል ለፕሮጀክቶቹ የጠየቁት መሬት እንዲተላለፍላቸው ከመወሰኑ በፊት በክልሉ መንግሥት ተገቢውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጧል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ያስመዘገቡት ካፒታልም በየዘርፉ ሲታይ፤ በግብርና 1 ነጥብ 82 ቢሊየን ብር፣ በኢንዱስትሪ 7 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር እንዲሁም በአገልግሎት 4 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
መሬት እንዲተላለፍላቸው የተወሰነላቸው ባለሃብቶች ያስመዘገቡት ካፒታል ካላፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ7 ነጥብ 18 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡
በሌላ በኩል 14 ነጥብ 621 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 187 ባለሀብቶች በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸው፤ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ለ25 ሺህ 416 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡
በአንጻሩ በገቡት ውል መሰረት ሳያለሙ ከተገኙ 158 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል ለ114ቱ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን፤ 44ቱ ውላቸው እንዲቋረጥና ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 12 ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሕብረተሰቡን በሥራ ዕድል፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.