የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 47ኛው የምዕራብ ዕዝ የምሥረታ በዓል “የፅናት ተምሳሌት፤ የኢትዮጵያ ጋሻ” በሚል መሪ ሐሳብ ፓናል ውይይትን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሠ እና የዕዙን ጨምሮ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አሻድሊ ሃሰን፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተገለጸው፤ ዕዙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሁም የሀገሪቱን ዳር ድምበር ለማስከበር በተሰለፈባቸው ግዳጆች ሁሉ ጀግንነቱን ማረጋገጡ ተነስቷል፡፡
ከፓናል ውይይቱ በኋላ የምዕራብ ዕዝን አርማ የማስተዋወቅ እና የዕዙ ጀብዶች ላይ ያጠነጠነ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በገላና ተስፋ