ሊቨርፑል በአርሰናል የክብር አቀባበል ይደረግለታል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ36ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ አርሰናልን ያስተናግዳል።
የሊጉ ጨዋታ ሳይጠናቀቅ አስቀድሞ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠዉ ሊቨርፑል በዛሬው ጨዋታ ወደ ሜዳ ሲገባ በተጋጣሚዉ አርሰናል የክብር አቀባበል ይደረግለታል።
በ82 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው ሊቨርፑል ሻምፒዮን መሆኑን አስቀድሞ ቢያረጋግጥም ነጥቡን ከፍ አድርጎ የውድድር ዘመኑን ለማጠናቀቅ ወሳኙን ሶስት ነጥብ ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር በፒኤስጂ የተሰናበተው አርሰናል በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በሻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ቦታ ለማግኘት እና ደረጃውን ለማስጠበቅ ይፋለማል።
በኤምሬትስ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የሊጉ ጨዋታ 2 አቻ በሆነ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል።
ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት
ኒውካስል ዩናይትድ እና ቼልሲ ቀን 8 ሰዓት ላይ በሴንት ጀምስ ፓርክ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ኒውካስል ዩናይትድ በ63 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቼልሲም በተመሳሳይ 63 ነጥብ በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሳምንቱ አጋማሽ በዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን ያረጋገጠው ማንቼስተር ዩናይትድ ቀን 10 ሰዓት ከ15 ላይ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ዌስትሀም ዩናይትድን ያስተናግዳል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በ39 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ዌስትሀም ዩናይትድ በ37 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኖቲንግሀም ፎረስት ከሌስተር ሲቲ እንዲሁም ቶተንሀም ሆትስፐር ከክሪስታል ፓላስ በተመሳሳይ ቀን 10 ሰዓት ከ 15 ላይ የሚደረጉ ሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው።