Fana: At a Speed of Life!

ዴንማርክ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ልማት ተግባራት መደገፏን እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ አጋርነት በሁሉን አቀፍ ልማት፣ በአረንጓዴ ሽግግር ውጥኖች እና ህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች፡፡

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ህዝብን የልማት ተነሳሽነት እና ሰው አክባሪነት ባህልን አድንቀዋል።

አምባሳደሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋትና ለማሳደግ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደውን የመሰረተ ልማት ሥራ አወድሰዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን በማስታወስ፤ ዴንማርክ በፈረንጆቹ 2018 የመጀመሪያውን የድጋፍ ፕሮግራም መተግበር ከጀመረች ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ትልቅ እመርታ አሳይቷል ብለዋል።

ሁለተኛውን ዙር የአምስት ዓመት የድጋፍ ፕሮግራም በቅርቡ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ በአቅም ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በውሃ ልማት፣ በዘላቂ ሃይል እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ግብርና እውን የማድረግ ጥረትን ለመደገፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጠናው ቁልፍ ተዋናይና የአፍሪካ ቀንድ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ በአህጉሪቱ የሰላምና መረጋጋት ሥራዎች የላቀ ሚና እየተወጣች መሆኗንም አስታውሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን ተግባራት አድንቀው፤ በተለይም በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለአህጉሪቱ ዜጎች ስደት እና ግጭት አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመከላከል በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ሀገራቸው በተለያዩ ዘርፎች ለመስራት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማስፋት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

ዴንማርክ ቁልፍ አጋር ሆና እንደምትቀጥል ለኢትዮጵያውያን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የዘላቂ ልማት ሥራ ሀገራቸው ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.