የአፍሪካ ህብረት ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቷ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያከነወነ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ባለፉት አምስት ወራት ህብረቱ ያከናወናቸውን ስራዎች እንዲሁም የተቋሙን የትኩረት አቅጣጫዎች እና ግቦች በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ ግጭቶች በንግግር እንዲፈቱ ህብረቱ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም በሶማሊያ ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በሶማሊያ ከተሰማራው የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ጋር ምክክር መደረጉን አስታውሰዋል።
በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ህብረቱ በጁባ ተገኝቶ በሁለቱ መሪዎቸ መካከል ቀደም ሲል የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን መጠየቁን ተናግረዋል፡፡
በሱዳንም በንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳትን ለመቀነስ እና የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የሰላም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።
በተጨማሪም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሚንቀሳቀሰው የኤም 23 ታጣቂ ቡድን ጋር በተያያዘ በሩዋንዳ እና በኮንጎ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እንዲረግብ ህብረቱ ከሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጋር መምከሩን ገልጸዋል።
ከሰላምና ፀጥታ ስራዎች በተጨማሪ ህብረቱ ቀጣናዊ ኢኒሼቲቮችን ለማጠናከር ከኢጋድ፣ ሳድክ፣ ኢኮዋስ እና ኮሜሳ ከመሳሰሉ ቀጣናዊ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ህብረቱ ከተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረገው ትብብር እንደሚጠናከር ጠቁመዋል።
በሚኪያስ አየለ