Fana: At a Speed of Life!

በእነ ብርቱካን የክስ መዝገብ በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦች የዋስትና ጥያቄ ከ2 ተከሳሾች ውጭ ያሉት ውድቅ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእነ ብርቱካን ተመስገን የክስ መዝገብ በሽብር ከተጠረጠሩ ግለሰቦች መካከል የ10ኛ እና 11ኛ ተካሳሾች የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ የሌሎቹ ውድቅ ተደረገ፡፡

ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር የወንጀል ችሎት ሲሆን፤ በዚሁ መሠረት የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ፤ መዓዛ መሐመድ፣ ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ኃ.የተ.የግ/ማኅበር፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ አመራሮች እና ብርቱካን ተመንስገንን ጨምሮ 16 ግለሰቦች ናቸው።

ዐቃቤ ሕግ ተፈጽሟል ባለው የወንጀል ድርጊት እንደየተሳትፏቸው ሦስት የተለያዩ ክሶችን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ-ሽብር የወንጀል ችሎት ክስ መስርቷል፡፡

በአንደኛው ክስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ) እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3/1/ለ/ ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ ከሌሎች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋር ሆነው፤ የፖለቲካ ዓላማን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ በሕገ መንግሥት የተቋቋመውን የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥትን በኃይል በማስወገድ ስልጣን መያዝ ይህ ካልሆነም መንግሥትን በኃይል በማስገደድ ለድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ የሚል ዓላማ ይዘው መንቀሳቀሳቸው በክሱ ተብራርቷል፡፡

በዋናነትም 6ኛ ተከሳሽ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆና በዩኒቨርሲቲው ተመድባ ባለችበት ተጠልፋ እንደተደፈረች በማስመሰል፤ ሐሰተኛ መታወቂያን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍና ዕቅድ አውጥቶ በመስጠትና በመተግባር በመሳተፋቸው ተከሳሾቹ በፈፀሙት የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

እንዲሁም ሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ7ኛ እስከ 11ኛ ተራ ቁጥር ባሉ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ነው፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፣ 34፣ 43 (3)፣ 46 እና የጥላቻ ንግግርን እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4፣ 5 እና 7/4 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከስሰዋል፡፡

7ኛ ተከሳሽ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ኃ.የተ.የግ/ማኅበር እና 8ኛ ተከሳሽ ሲልቨር ስፕሪንግ ፕሮዳክሽን እና ፕሮሞሽን ኃ.የተ.የግ.ማኅበር (የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን እህት ኩባንያ) እንዲሁም 9ኛ ተከሳሽ ማክዳ ፍስሐጽዮን (ማክዳ አሰፋ)፤ በኢ.ቢኤስ ቴሌቪዥን የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም የሕግ ክፍል አስተያየትንና የሥራ ኃላፊነቷን ወደ ጎን በመተው ትክክለኛ ያልሆነ የተቀነባበረ ታሪክ በቀን 14/7/2017 ዓ.ም በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን አዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም አማካይነት ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረጓ ክሱ ተመስርቶባታል።

10ኛ ተከሳሽ ታሪኩ ኃይሌ ረታ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዳይሬክተር እና 11ኛ ተከሳሽ ህሊና ታረቀኝ ረዳት ዳይሬክተር 6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገንን በአካል ያገኟት በመሆኑ ታሪኩ ውስጥ ብዙ የሚያጠራጥሩ እውነት የማይመስሉ ንግግሮች እያሉ፣ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ እየቻሉ ይህን ባለማድረግ ግብረአበር በመሆን በፈፀሙት የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ወንጀል ተከስሰዋል፡፡

እንዲሁም ሦስተኛው ክስ በ3ኛ፣ በ6ኛ እና ከ12ኛ እስከ 16ኛ ተራ ቁጥር ባሉ ተከሳሾች ላይ የቀረበ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 (2) በመተላለፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፣ በወንጀሉ ድርጊት እና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ለ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን የማይገባትን 3 ሚሊየን 109 ሺህ 882 ብር ከ45 ሳንቲም በመጋቢት ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም ከተለያዩ ግለሰቦች ወደ ባንክ ሂሳብ ቁጥሯ እንዲገባላት ሁኔታ ያመቻቹ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚህም ተከሳሾቹ በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሽብር የወንጀል ችሎት በዛሬ ውሎው የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ የተመለከተ ክርክርን አዳምጦ በ1ኛ እና በ3ኛ ክስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች የተከሰሱበት የሕግ ድንጋጌ የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

እንዲሁም በ2ኛ ክስ የተከሰሱት የኢ.ቢኤስ ቴሌቪዥን ባልደረቦች 10ኛ ታሪኩ ኃይሌ እና 11ኛ ህሊና ታረቀኝ የተከሰሱበት የሕግ ድንጋጌ የዋስትና መብት የማያስከለከል በመሆኑ በ25 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኗል፡፡

በሲፈን መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.