በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር በጊዜ እንዲገታና በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ።
የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በእንጅባራ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት እና የግል ኮሌጆች ምሁራን ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች እና በተፈጠረው ግጭት የደረሰው ጉዳት እንዲሁም ከችግሩ መውጫ መንገዶች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ሰውነት በወቅቱ እንደገለጹት፤ የተፈጠረው ችግር ኅብረተሰቡ ለዘመናት ለፍቶ የገነባቸውን ተቋማት ያወደመ፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች ዘንድ የቆዩ መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ ያደረገ ነው።
በየደረጃው በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ኅብረተሰቡ ችግሩ ያስከተለውን ጉዳት በውል የተረዳበት እና ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየበት መሆኑን አንስተዋል።
የኅብረተሰቡን አጋርነት ከጸጥታ መዋቅሩ ቁርጠኝነት ጋር በማቀናጀት ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው፤ ግጭቱ ካደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የክልሉን እድገት እየገታ ነው ብለዋል።
ይህም በጊዜ ካልተገታ የሚያደርሰው ሁለንተናዊ ቀውስ የከፋ እንደሚሆን በማንሳት ምሁራን ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስገንዘባቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።