የአፍሪካ ህብረት የሃይማኖት ተቋማት የሚያደርጉትን የሰላም ውይይትና አብሮነት ይደግፋል – መሃሙድ አሊ ዩሱፍ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የሃይማኖት ተቋማት የሚያደርጉትን የሰላም ውይይትና አብሮነት ይደግፋል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ተናግረዋል።
በ3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ላይ ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ለሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት እውን መሆን የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ዓላማቸውን ሊያሳኩ የሚፈልጉ ጽንፈኞችና አሸባሪዎችን በጋራ መከላከል ከእምነት ተቋማት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት ለሌሎች በአርአያነት የምትጠቀስ መሆኗንም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የሚፈለገውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት የሃይማኖት ተቋማት የሚያደርጉትን የሰላም ውይይትና አብሮነት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የሃይማኖት መከባበርና አብሮነት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የብሄር ነፃነትና እኩልነት እውን የሆነባት እንዲሁም አንዱ ሌላውን አክብሮ የሚኖርባት ሀገር ናት ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተለያዩ ሃይማኖቶች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ የሚሰሩትን ተግባር እንዲያጠናክሩ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዜጎች አብሮነትና በትጋት መስራት ለዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች በትብብር መፍትሄ መስጠት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ጭምር ስለ ሃይማኖቶች እኩልነት መንግስትና ሃይማኖት መለያየት በግልጽ አስቀምጣ እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።