ዓመታዊው የርክበ ካኅናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡
አቡነ ማትያስ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለሕዝበ እግዚአብሔር የምናበረክተው አገልግሎት በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን፤ በኢኮኖሚውና በማኀበራዊው አገልግሎትም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ሕዝባችን የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በኢኮኖሚውም ከድህነት የተላቀቀ እንዲሆን በተግባር በመሳተፍ አርኣያ ሆነን መሥራት ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
እንደሀገርም ሁሉን የሚያግባባ ሐሳብ በመፈለግ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት በዚህ አማራጭ ኢትዮጵያ እፎይታ እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ጉባዔው፤ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አሥተዳደራዊ አፈፃፀም በመገምገም የሥራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ