ክሪስታል ፓላስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን አነሳ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ዋንጫ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ ማንቼስተር ሲቲን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን አንስቷል፡፡
በግዙፉ የእንግሊዝ ዌምብሌይ ስታዲየም የተካሄደውን የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው ቢሆንም 17ኛው ደቂቃ ላይ ኤዜ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ ክሪስታል ፓላስ ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቅቋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ክሪስታል ፓላስ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ዋንጫ ማሳካት ችሏል፡፡
ውሃ ሰማያዊዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ክሪስታል ፓላስ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የተከላካይ መስመሩን በመስበር ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ክሪስታል ፓላስ የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ማሸነፉን ተከትሎ የአውሮፓ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡