በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ዝግጁ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ2017/18 መኸር እርሻ እስካሁን 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ዝግጁ መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ፈቃዱ ወዬሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በመኸር እርሻ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በላይ ማሣ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ዝግጅቱ ሜካናይዝድ እርሻን ጨምሮ እየተከናወነ ገልጸው፤ ከመኸር እርሻ 55 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
እስካሁን 1 ሚሊየን 20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ዝግጁ ተደርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ማሽላ፣ በቆሎ እና ሌሎች ሰብሎች እንደሚዘሩ አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ ማሣውን ተስማሚ በሆኑ ሰብሎች በመሸፈን ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በፍጥነት ለማሰራጨት በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ