29 የዓሣ ዝርያዎች በሕዳሴ ግድብ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 29 ዓይነት የዓሣ ዝርያዎች መኖራቸውን የጥናት ውጤት አመላከተ፡፡
ከእነዚህ መካከል በብዛት የሚገኙትና ለገበያ የሚቀርቡት አራት ዓይነት መሆናቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ባበክር ኸሊፋ አብራርተዋል፡፡
በምርት ደረጃ በከፍተኛ መጠን የሚገኙት የዓሣ ዝርያዎችም፤ ቆሮሶ፣ አምባዛ፣ ዱባ እና ናይል ፐርች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ምርቱም ለአካባቢው፣ አሶሳ እና አዲስ አበባ ከተሞች ገበያ እየቀረበ መሆኑን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡
የምርቱ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ናይል ፐርች የተባለው የዓሣ ዝርያ በውጭ ሀገራት ገበያ ጭምር በእጅጉ ከፍተኛ ፍላጎት አለ ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ገበያ ፍላጎትን ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን የዓሣዎች ክብደት እንደዝርያቸው ቢለያይም፤ እስከ አሁን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቁ ሆኖ የተመዘገበው 80 ኪሎ ግራም የሚመዝን የናይል ፐርች ዓሣ ዝርያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ከ4 እስከ 15 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው