በርካታ ትሩፋቶችን ያበረከተው ፎረም
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም በርካታ ትሩፋቶችን በማስገኘት በስኬት መካሄዱን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
ፎረሙ 120 የሀገር ውስጥ እና በርካታ የውጭ ሀገራት የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን ወደ አንድ ማምጣቱን በብሔራዊ ባንክ የባንኮች ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው ገልጸዋል፡፡
በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እየተተገበሩ የሚገኙ ሥራዎችን በማሳየት ብሎም በፋይናንስ ተቋማት መካከል የልምድ መለዋወጫ ዕድል በመፍጠር ረገድም ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ከመደረጉ ጋር ተያይዞ የሚወጡ የሕግ ማዕቀፎችን አስመልክቶ በቀጥታ ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻር እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻውን በተመለከተም ለፎረሙ ተሳተፊዎች በአግባቡ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በፎረሙ ላይ ከተገኙ ዓለም አቀፍ ባንኮች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ያሳወቁ አሉ ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ ዓለም ባንክ እና የልማት አጋር አካላት ያደረጉት ድጋፍ በኢትዮጵያ ያመጣውን ለውጥ እንዲረዱ፤ በቀጣይም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የውጭ ሀገራት ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ፤ የባንክ ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ የውጭ ካፒታል ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እና ኢንቨስተሮች እንዲሳቡ ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የውጪ ባንኮች ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በጋራ የሚሠሩበትን ዐውድ ለመፍጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፤ ለመድረኩ ተሳታፊ የፋይናንስ ተቋማትም ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ፎረሙ ለባለድርሻ አካላት በመረጃ በተደገፈ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ግንዛቤ በመፍጠር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ነው ያስታወቁት፡፡
በዮናስ ጌትነት