Fana: At a Speed of Life!

በጅማ ዞን የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትግበራ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጅማ ዞን እየተከናወነ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትግበራ አበረታችና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

ባለፋት ዘጠኝ ወራት የሌማት ትሩፋት፣ የምግብ ሥርዓት ሽግግርና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስራ አፈጻጸም ግምገማ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች በጅማ ዞን ወረዳዎች በሌማት ትሩፋት የተከናወኑ ዘመናዊ ቀፎ የማር ምርት ልማት፣ የአቮካዶ፣ የሙዝ ተክል ልማት፣ የሻይ ቅጠል ችግኝ ዝግጅት እና የዶሮና እንቁላል ምርት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዞኑ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በትኩረት እየተተገበረ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ዞኑ ያለውን አመቺ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ለማር ምርት የተሰጠውን ትኩረት ጨምሮ በሌማት ትሩፋት ያለው እንቅስቃሴ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው÷ በማር፣ በአሳ እርባታና በዶሮና እንቁላል እንዲሁም በፍራፍሬ ልማት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ በጅማ ዞን በሌማት ትሩፋት በርካታ የምርት አይነቶች ላይ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተመልክተናል ነው ያሉት።

የተመለከቷቸው የዘመናዊ ቀፎ የማር ኢኒሼቲቭ፣ የአቮካዶ ልማት እና ሌሎችም የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተስፋ ሰጪና ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልልም የተለያዩ የሌማት ትሩፋት የልማት ስራዎች በትኩረትና በከፍተኛ ክትትል እየተሰሩ መሆኑን አንስተው÷ በዚህም የተሟላ የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.