Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች የሚገኘው ገቢ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናስር አህመድ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ ህያው ቅርስ የሆነችውን የሐረር ከተማን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረትና በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ በተሰሩ ሥራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ሐረርን ለመጎብኘት እየመጡ ነው ብለዋል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ በመቶ ሺዎች ብር ብቻ የሚቆጠር እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ብቻ ከ7 ሺህ የሚበልጡ የውጪ ሀገራት እና ከ121 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መጎብኘታቸውን እና በዚህም ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።

የሐረር ከተማ ከወር በፊት የዓለም የቱሪዝም ከተሞች ፌዴሬሽን አባል መሆኗ በቀጣይ የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር የዘርፉን ገቢ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ክልሉ የዘርፉን ገቢ በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የቱሪስት መስህቦችን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በያሲን ሸምሱዲን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.