የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብራዚል አይነተኛ ምሳሌ ናት – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ብራዚል በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ስኬት አይነተኛ ምሳሌ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ ከ2ኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መዋጋትና የገጠር ልማት ጉባኤ ጎን ለጎን ሀገሪቱን በግብርና ዘርፍ ስኬታማ ያደረጉ ተቋማትን ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱም የብራዚል ብሔራዊ አቅርቦት ኩባንያ የስራ እንቅስቃሴን ተመልክቷል፡፡
በዚሁ ወቅትም ኩባንያው ከምርት እስከ ገበያ ባለው ሂደት የአቅርቦት አስተዳደርን የሚከታተልበት አሰራር ሰፊ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ልዑኩ አፈርን አክሞ ምርታማነትን በመጨመር፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን በማዘጋጀትና ዘላቂ የግጦሽ አያያዝን በማሻሻል ለሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ቁልፍ ሚና እንዳለው የተነገረለትን የብራዚል የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን ጎብኝቷል፡፡
ተቋሙ አርሶ አደሩ በፈጠራና ቴክኖሎጅ የተደገፉ ስራዎችን እንዲሰራ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በተለያዩ የስራ መስኮች ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኅብረት ስራ ማህበር የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
አቶ ተመስገን በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ እና ብራዚል ተመሳሳይ የአየር ጸባይና አሲዳማ አፈር እንዲሁም የሚጋሯቸው የተፈጥሮ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
አክለውም፤ ብራዚል በዘርፉ ባላት ስኬት የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት አይነተኛ ምሳሌ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግብርናውን ለማሳደግና በአረንጓዴ አሻራ ተፈጥሮን ለማከም አዲስ ፖሊሲ ቀርጻ እያከናወነቻቸው ያሉ ሁለንተናዊ ተግባራት ከብራዚል አድናቆት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በብራዚል የትብብር ኤጀንሲ አማካኝነት በደን አስተዳደርና የአሲዳማ አፈር ፕሮጀክት የተፈራረሙት ስምምነት በትግበራ ላይ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው