የኢትዮጵያ አትሌቶች ከትራክ ወደ ጎዳና ውድድሮች ፍልሰት …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች ወደ ጎዳና ውድድሮች እያመሩ መሆናቸው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ንጉሴ ጊቻሞ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ አትሌቶች በትራክ ውድድሮች ላይ ራሳቸውን በሚገባ ሳያጠናክሩና ሰውነታቸውን ሳያዳብሩ ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች አየፈለሱ ነው።
ይህም ጊዜያዊ ጥቅምን ብቻ ለማግኘት የሚደረግና ሀገርንና አትሌቶቹንም ጭምር የሚጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ መምህርና በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ በበኩላቸው÷ ችግሩ እንደ ሀገር አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ በትራክ ውድድሮች የውጤት መቀዛቀዝ እየታዬ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትራክ ውድድሮች ተሳታፊዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የጎዳና ላይ ውድድሮች የሚያስገኙት የሽልማት ገንዘብ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የትራክ ተሳታፊዎች እጥረት አትሌቶች በቶሎ ወደ ጎዳና ውድድሮች መውጣት እንደሆነም በምክንያትነት አንስተዋል።
ችግሩ እንደ ሀገር በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት በጊዜ ሂደት ተሰጥዖን አውጥቶ በአግባቡ የመጠቀም አቅምን እንደምገድብም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል።
በዳዊት ደያሳ