Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሚሊየን በላይ ህፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ተከተቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከግንቦት 6 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ እስካሁን 1 ሚሊየን 31 ሺህ 306 ህፃናት መከተባቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ እንደተናገሩት፤ ክትባቱ ከ9 ወር እስከ 59 ወር ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ህፃናት የሚሰጥ ነው።

በዘመቻው ከዕቅድ በላይ ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ከኩፍኝ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ ሌሎች የክትባት ሥራዎችም በዘመቻው ወቅት እየተከናወኑ እንደሆነ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በዚህም በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች በተለያየ ጊዜ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል የተቀናጀ የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ከተወለዱ ጀምሮ ምንም ክትባት ያልወሰዱ 1 ሺህ 807 ህፃናትን እንዲሁም ጀምረው ያቋረጡ 1 ሺህ 983 ህጻናትን በመለየት ክትባት የማስጀመር ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

በዘመቻው ወቅት በክልሉ 224 ሺህ 606 አጥቢ እና ነፍሰጡር እናቶችን እንዲሁም 1 ሚሊየን 994 ሺህ 631 ህጻናት የሥርዓተ ምግብ ልየታ መደረጉን፣ 944 ሺህ 589 ዕድሜያቸው ከ6 ወር በላይ ለሆናቸው ህጻናት የቫይታሚን ኤ እደላ መደረጉን አመላክተዋል።

አስፈላጊ ክትባቶችን መስጠትን ጨምሮ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ቀጣይነት ያለው ሥራ እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ አደረጃጀቶች እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.