ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት10 ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ገለጸ።
የጽ/ቤቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን ዳንኤል ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ለህዳሴ ግድቡ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል።
በዚህም ባለፉት 10 ወራት ከህብረተሰቡ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልፀው፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በጠቅላላው ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ስኬታማ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ይህንን ፕሮጀክት አጠናቀን ሪቫን ልንቆርጥ ተቃርበናል ሲሉ ተናግረዋል።
ለፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ መድረስ የመንግስትና የህዝቡ የጋራ ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሞራል፣ በዕውቀትና ሙያ በርካታ ድጋፎች መደረጋቸውን አስረድተዋል።
ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ በቦንድ ግዢ እና ስጦታ በማበርከት፣ 8100 ላይ A ብሎ በመላክ ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ዳያስፖራው በኦንላይን ሃብት ለማሰባሰብ በተዘጋጀው ፕላት ፎርም itismydam.com ወይም በኢትዮ ዳይሬክት የሞባይል መተግበሪያ (Ethio-direct) ወይም በቴሌ ብር ድጋፍ ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን አስታውሰዋል።
በመሳፍንት እያዩ