Fana: At a Speed of Life!

በዘርፉ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

“በዲጂታል የታገዘ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ” በሚል መሪ ሐሳብ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮችን፣ የልማት አጋሮችን፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችን እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተጨባጭ ለውጥ ከመጣባቸው ዘርፎች ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አንዱ ነው።

ዘርፉን በዲጂታል ለማዘመን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው÷ በመንግሥትና በግል አጋርነት የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሳልጡ ቴክኖሎጂዎች መተግበራቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የዲጂታል ትራንስፖርት ማዕቀፍ፣ ስማርት መሰረተ ልማት፣ ዲጂታል የነዳጅ የክፍያ ሥርዓት፣ ዲጂታል የትኬት መቁረጫና የክፍያ ዘዴ፣ ስማርት የመኪና ማቆሚያዎችና ዲጂታል የትራፊክ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋታቸውን አንስተዋል።

በስትራቴጂክ ሪፎርም የተደገፉ አገልግሎትን የማዘመንና የማሻሻል ስራዎች የዘርፉን አጠቃላይ እንቅስቃሴና እድገት እየቀየሩት መሆኑን አንስተው÷ የዲጂታል ክህሎት፣ መሰረተ ልማት፣ የሳይበር ደህንነትና ሌሎች ተግባራትን አጠናክሮ ለመጠቀል የመንግሥትና የግሉ አጋርነት መጠናከር አለበት ብለዋል።

ዲጂታል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለሚደረገው ሽግግር ወሳኝ በመሆናቸው የቅንጅት ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.