Fana: At a Speed of Life!

ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች የተሳተፉበት የመላው አማራ ጨዋታዎች ውድድር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደሴ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 9ኛው መላው አማራ ጨዋታዎች ውድድር በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

ከግንቦት 3/2017 ዓ.ም ጀምሮ “ስፖርት ለሰላም፤ ሰላም ለሁሉም” በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ በቆየው ውድድር÷ በ19 የስፖርት አይነቶች ከ18 ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በመዝጊያው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ ውድድሩ ባለፉት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የክልሉን ስፖርት በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረው ገልጸዋል።

ተተኪ ስፖርተኞችን እና በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ከማፍራት አንጻር ያለው አበርክቶ የላቀ መሆኑንም ጠቁመው÷ ስፖርትን የሰላም መሳሪያ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው÷ ውድድሩ ከስፖርታዊ ክዋኔነቱ ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የስፖርት ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋ የጸጥታ መዋቅር፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የከተማዋ አመራር፣ ነጋዴዎችና የደሴ ከተማ ነዋሪ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በሙሉቀን አበበ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.