Fana: At a Speed of Life!

የማዕከሉ መመስረት የሠራዊቱን የሥራ ፈጠራ አቅም የሚያጎላ ነው – አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ የኢንተርፕርነርሽፕ እና ኢኖቬሽን ማዕከል መመስረት የሠራዊት አባላትን ዕምቅ የሥራ ፈጠራ አቅምና ችሎታ የሚያወጣ ብሎም የተደበቀ የፈጠራ ባለቤትነታቸውን የሚያጎላ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ተናገሩ።

ሚኒስትሯ የማዕከሉን ምስረታ አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፤ ማዕከሉ የሠራዊቱ አባላትን የተደበቀ የፈጠራ ባለቤትነታቸውን የሚያጎላ እንዲሁም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከቋሚ ተጧሪነት በማላቀቅ ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ትልቅ አቅም የሚሆኑበትን ዕድል የሚያመቻች ነው ብለዋል።

የማዕከሉ ምስረታ በመከላከያ ሠራዊት ጉዞ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የሚቀመጥና የሪፎርም አንድ አካል ነው በማለት ገልጸው፤ የዛሬው ቀን ማዕከሉ መቋቋሙን የምናበስርበትና መዋቅራዊ ስኬቱን የምንገልጽበት አጋጣሚ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ ደግሞ እንደ ሀገር የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላበረከቱት ጽኑ አገልግሎት፣ ክብር መስዋዕትነትና የዕድሜ ልክ ቁርጠኝነት ምላሽ የምንሰጥበትና ለተከፈለው በቃላት የማይገለጽ ዋጋም ዕውቅና የምንሰጥበት ነው በማለት ተናግረዋል።

ዕውቅናው ድካምና መስዋዕትነታቸውን ወደ ሌላ ህያው ትሩፋት በማሸጋገር የሚገለጽ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከሉ መመስረት ሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ የሠራዊት አባላትን በማስታወስ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በሚሆን መልኩ ምላሿን የሰጠችበት ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የሰራዊቱ አባላት ከውትድርና መልስ የአገልግሎት ትሩፋታቸውን በማራዘም አዳዲስ ሥራዎችን በመፍጠር፣ አዳዲስ የሥራ መስኮችን በማንቀሳቀስ ሀገራቸውን እንዲገነቡና ቤተሰባቸውን እንዲደግፉ ብሎም አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችል ታላቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።

የማዕከሉ መመስረት ለሠራዊታችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት ወደ ተግባር የምንለውጥበት ትልቅ ዕድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው በማለት ገልጸው፤ የመንግስትና የግል ተቋማት ለማዕከሉ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.