ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከመሰል ተቋማት ጋር እንሠራለን- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይን ዕውን ለማድረግ በፈጠራና ቴክኖሎጅ የታገዘ ሥራን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ ከመሰል ተቋማት ጋር የመሥራት መርህ እንደምትከተል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በብራዚል ሳኦ ፖሎ የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች የሥራ እንቅስቃሴን ከጎበኙ በኋላ ስኬታማ ውይይቶች አድርገዋል፡፡
በጉብኝታቸውም፤ የንግድ፣ ወታደራዊና የግብርና ዘርፍ የሚደግፉ አውሮፕላኖች አምራች የሆነውን ኢምብራኤር ኩባንያ ተመልክተዋል፡፡
ኩባንያው በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በትብብርና በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳለው መገንዘባቸውን አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የሳኦ ጆዜ ዶስ ካምፖስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ፓርክን የጎበኙ ሲሆን፤ ፓርኩ የፈጠራ ሐሳብን ለለውጥና ችግር ፈች መፍትሄ በሚያመጡ ስታርት አፖች፣ መካከለኛና ከፍተኛ የተግባር ተኮር ስራዎች ዙሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘረጋ የዘርፉ ስራ ሂደት ያለው ተሳትፎ ሰፊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይን ዕውን ለማድረግ በፈጠራና ቴክኖሎጅ የታገዘ ስራን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያም፤ ከመሰል ተቋማት ጋር በጋራ የመስራት መርህ ትከተላለች ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
ፓርኩ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የሰጠችውን ትኩረት ማድነቁን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ባለሙያን ማብቃት ላይ ተቀራርበን የምንሰራባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠናል ብለዋል፡፡