Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው የፈረንሳይ ቆይታ ስኬት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በፈረንሳይ-ፓሪስ ያደረገው ጉብኝት እና ውይይት ስኬታማ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ገለጹ፡፡

የልዑኩን የፈረንሳይ ጉብኝት አስመልክተው ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ጉብኝቱ ፕሬዚዳንት ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙ በጥቂት ወራት ውስጥ የተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚሁ መሠረትም ጉብኝቱ በአዲስ አበባ የተጀመሩ፣ ውይይት የተካሄደባቸው እና መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮችን ተከትሎ የተካሄደ እና አፈጻጸማቸውን ብሎም የደረሱበትን ደረጃ ለመገምገም የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በፈረንሳይ የተደረገው ጉብኝትና ውይይት በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለ ትብብር እና ኢንቨስትመንትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ቀደም ብሎ በተደረሰ መግባባት መሠረት ያለንበትን ደረጃ ለማየት ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

የፈረንሳይ ባለሃብቶችን እና ድርጅቶችን ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ከፍ ለማድረግ ዘላቂ የረጅም ጊዜ ፋይዳ ያላቸው ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት የሚቻልበትን አግባብ ያሳየ ውይይት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ትብብር እና ትስስር ምን መምሰል እንዳለበት ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የተደረገበት መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በቀጣናው ያለ የጸጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ምክክር የተደረገበት እና በሁለቱ ሀገራት መካከል በመተባበር የቀጣና ሠላምን ከፍ ለማድረግ እንዴት እንደሚቻል ምክክር የተካሄደበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.