በቂ የእንቁላል ምርት አቅርቦት እንዲኖር እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተከሰተውን የእንቁላል ዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት በእሁድ ገበያዎች በቂ የእንቁላል ምርት አቅርቦት እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባደረገው ቅኝት አንድ እንቁላል ከ20 እስከ 21 ብር እየተሸጠ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የዋጋ ጭማሪውን ለማረጋጋት ምን እየተሠራ እንደሆነ ጣቢያችን ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አሸናፊ ብርሃኑ፤ ለእንቁላል ዋጋ መናር ዋናው ምክንያት የመኖ ዋጋ መጨመር ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የበዓላት መደራረብ የእንቁላል ምርት እጥረት እና ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም በ210 የእሁድ ገበያዎች በስፋት የእንቁላል ምርት አቅርቦት እንዲኖር ከአምራቾች ጋር ትስስር በመፍጠር ገበያውን ለማረጋጋት እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በእጸገነት አመሃ