በቀይ ባሕር ቀጣና የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እደግፋለሁ – የአፍሪካ ኅብረት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት በቀይ ባሕር ቀጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሙሉ በሙሉ ይደግፋል አሉ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሀሙድ አሊ ዩሱፍ።
ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ፥ ለዓለም የንግድ እንቅስቃሴ እጅግ ስትራቴጂያዊ በሆነው የቀይ ባሕር የውኃ መስመር በንግድ መርከቦች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጥቃቶች ለቀጣናው ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኅብረቱ በቀይ ባሕርና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ አስተማማኝ ደኅንነትን ለመገንባት በሰላማዊ መንገድ የሚደረጉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶችን ይደግፋል ነው ያሉት።
ሊቀመንበሩ ሁቲዎች በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ላይ የባሕር ላይ እገዳ መጣላቸውን ካወጁ በኋላ በቀይ ባሕር በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት አጥብቀው አውግዘዋል።
በቀይ ባሕር ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለትን፣ የነዳጅ ዋስትናን እና የአፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው መሰል ጥቃቶች እንዲቆሙና ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲከበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሶስና አለማየሁ