Fana: At a Speed of Life!

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ላለፉት 15 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ2017 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ተጠናቀቀ፡፡

ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ፀሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሰጡት መግለጫ፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚካሄዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔዎች አንዱ የሆነው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ምልዓተ ጉባዔው፤ በቤተክርስቲያኗ፣ ሀገራዊና ወቅታዊ ዐበይት ጉዳዮች ላይ መወያየቱን እና 16 ውሳኔዎችን ማሳለፉንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በሰላም እና በንግግር እንፈታ ዘንድ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አስትላለፋለች ብለዋል::

ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ የቤተ ክርስቲያኗ ይዞታዎችን መልሶ በመገንባት እና ምትክ በመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላደረጉት ትብብር አመሥግነዋል፡፡

ምል ዓተ ጉባዔው የቤተ ክርስቲያኗ በጀት 5 ነጥብ አራት ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉንም አስታውቀዋል፡፡

ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ያፈነገጡ ስብከቶችን ሲሰጡ የነበሩ አባቶች ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ርክበ ጉባዔው መወሰኑንም ገልጸዋል፡፡

ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ብጹእ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እንዲሁም ብጹእ አቡነ ህርያቆስ የአዲስ አበባ፣ ሀድያ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን በርክበ ጉባዔው መሾማቸው ተጠቅሷል፡፡

በጸጋዬ ንጉስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.