ኤሌክትሮኒክ የምክረ ሐሳብ መስጫ የዜጎችን ተሳትፎ ያሳድጋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ኤሌክትሮኒክ የሕዝብ ምክረ ሐሳብ መስጫና መቀበያ ሥርዓት በረቂቅ ሕጎች የዝግጅት ሂደት የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግ ግልፅና ጠንካራ ሕጎችን ለማውጣት ያስችላል አሉ፡፡
ሕብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በረቂቅ ሕግ ላይ ሐሳብ እና አስተያየት የሚሰጡበት ኤሌክትሮኒክ (የበይነ መረብ) የሕዝብ ምክረ ሐሳብ መስጫ ሥርዓት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ እንዳሉት፤ በፍትሕ ሥርዓቱ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያድግ እና እንዲጠናከር በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
ኤሌክትሮኒክ የምክረ ሐሳብ መስጫ ሥርዓቱም በሕግ ዝግጅት ላይ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የአሠራር ሥርዓቱ ዜጎች በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው በረቂቅ ሕጎች ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማት ሕጎችን በሚያዘጋጁበት ወቅት የአሠራር ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ ዜጎች በአግባቡ እንዲሳተፉ መሥራት እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት፡፡