Fana: At a Speed of Life!

ከከርሠ ምድር እስከ ህዋ አሥፈላጊ መረጃዎችን በመተንተን የተሠሩ ሥራዎች መሠረት ጥለዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስፔስ ሣይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት ቢሆንም ከከርሠምድር እስከ ህዋ ለልማት አሥፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመለየት እና በመተንተን ያከናወናቸው ሥራዎች በዘርፉ መሠረት የጣለ ሆኗል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ ነገን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየሠራች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተቋቋመ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከከርሠ ምድር እስከ ስፔስ ድረስ ለልማት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እያቀረበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በከርሠ ምድር ጥናትና ምርምር የከርሠ ምድር የውኃ ሃብት ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም እና የኢትዮጵያ ሐይቆች ያሉበትን ሁኔታ የማጥናት ብሎም የውኃ ሃብቶችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በገጸ-ምድር ላይ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ሽፋን፣ የውኃና የአፈር ፀባይ በመለየት ለልማት አመች የሆኑ ወሳኝ መረጃዎችን እያመነጨ ነው ብለዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ በውኃና በመሬት ልማት ጥናትና መረጃ አያያዝ ተስፋ ሰጪ ዕውቀት እየተገነባ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካርታን በማተም ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ በመተግበሪያ ልማት ጭምር የሚደነቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱን መቋቋም ተከትሎ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስፔስ ክለብን መቀላቀሏን ጠቅሰው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሁለት ሳተላይቶችን ማምጠቋን አውስተዋል።

በቀጣይም ሦስተኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በሰው ሃብት ልማት ላይ ተጨባጭ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ከማስተማር ባለፈ ፍላጎትና ክኅሎት ያላቸውን ሕጻናትን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ይህም ነገን ታሳቢ ያደረገ ትጋት መሆኑን አስረድተው፤ ለሥራ ገበያው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል ዐውድ እየተፈጠረ እንደሚገኝ በጉብኝታቸው መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡

የእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ አቅምን በማሳደግ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር መሥራት የሚያስችል አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢንስቲትዩቱ መረጃዎች በመተማመን እየተጠቀሟቸው መሆኑን ገልጸው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህን መመልከት ደስታ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

ትውልድን ለማስቀጠል ታስቦ ሊሠራ ይገባል በሚል መርኅ የወል ሃብትና ተቋማትን በመገንባት ቀጣይነት ያለው የምርታማነት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

የስፔስ ሳይንስ፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የሳይበር ደኅንነትና የትምህርት ተቋማትም ሕጻናት ላይ በትኩረት ከሠሩ የሀገርን ህልም መፍታት እንደሚችሉ ነው ያስገነዘቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.