በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሃብትን ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም የመቀየር ጥረት …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመቀየር እየሰራሁ ነው አለ የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዳይሬክተር አሸናፊ ሃብቴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋፋት እና ነባሮችን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው።
በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በሚካሄደው የቱሪዝም ሳምንት መርሐ ግብር የክልሉ የቱሪስት መስህቦች በሚገባ መተዋወቃቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በክልሉ የቱሪስቶችን ቆይታ ጊዜ ለማራዘም ለጎብኚዎች ዘመኑን የዋጀና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
አገልግሎት አሰጣጡ የዲጂል ሥርዓትን የተከተለና እና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ እንዲሆን ከአስጎብኚ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አሸናፊ ሃብቴ አንስተዋል፡፡
ለውጪ ቱሪስቶች የተጋነነ ዋጋ በሚያስከፍሉ አስጎብኚ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎችና ተቋማት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም በዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች መደበኛ ክትትል እንዲሁም ጎብኚዎች በክልሉ በሚገኙ 23 ማዕከላት ስለ ቆይታቸው ግብረ መልስ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የቱሪስቶችን ቆይታ ደስተኛ እና አይረሴ ለማድረግ የቱሪዝም ምርት ስብጥር አቅርቦትን ለማሳደግ ትኩረት በማድረግ በፍላጎታቸው መሰረት የሚመርጧቸውን ቦታዎች እንዲመለከቱ ለአስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት አቅጣጫ ተቀምጧል።
የቱሪስቶች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆንም የቱሪስት መዳረሻዎች መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በመላኩ ገድፍ