Fana: At a Speed of Life!

በአውቶቡስ አገልግሎት ላይ የተደረገው የሰዓት ማሻሻያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በከተማ በአውቶቡስ አገልግሎት ላይ የተደረገው የሰዓት ማሻሻያ ሕብረተሰቡ አምሽቶ ሳይቸገር ወደ ቤቱ እንዲመለስ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሲስተምና ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰብስባቸው መንግስቴ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ መዲናዋ እያደገችና አምሽቶ የመስራት እንቅስቃሴ እየጨመረ በመምጣቱ የሰዓት ማሻሻያው አስፈልጓል።

በዚህም ሕብረተሰቡ በትራንስፖርት እጥረት የሚቸገርባቸውን መስመሮች በመለየት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ማሻሻያው ሲጀመር በተመረጡ 19 መስመሮች አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ጠቅሰው ÷ አሁን ላይ ወደ 27 መስመሮች ማደጉንና በቀጣይ የነዋሪዎችን ችግር በሚያቃልል መልኩ ተጠናክሮ እንደቀሚቀጥል ጠቁመዋል።

የሚሰማሩ የአውቶቡሶች ምልልስና ቁጥር መጨመሩን የገለጹት አቶ ሰብስባቸው÷አሁን ላይ በተመረጡ መስመሮች 120 አውቶቡሶች አገልግሎቱ እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የአገልግሎቱ መሻሻል በምሽት የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር መቅረፉን ጠቁመው÷በዚህም የከተማዋ ነዋሪ በምሽት ሥራውን አከናውኖ ሳይቸገር ወደ ቤቱ እንዲመለስ መድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.