Fana: At a Speed of Life!

የካንሰር በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የአቅም ማጎልበት ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጤና ሚኒስቴር የተለያዩ የካንሰር በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የሚያስችሉ የአቅም ማጎልበት ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአእምሮ ጤና መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ዘመናዊ የካንሰር የጨረር ሕክምና የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ሆስፒታሎቹም፤ ሐሮማያ፣ ጅማ፣ ሐዋሳ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ መቐለ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የማስማሪያ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡

በሆስፒታሎቹ የካንሰር የጨረር ሕክምናን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የግንባታና ማሽን ተከላ ተጠናቅቆ አራቱ ተቋማት በሥራ ላይ መሆናቸውን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ፈቃድ አግኝቷል ብለዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የካንሰር የአምስት ዓመት ዕቅድ ክለሳ ተደርጎ የካንሰር በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በ33 የመንግሥት ሆስፒታሎች የኬሞቴራፒ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የካንሰር መድኃኒቶች የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተጠብቆ በአግባቡ ለተጠቃሚ የሚደርስበትን ሂደት ለማገዝ በየዓመቱ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ የታካሚዎቹን የመድኃኒት ወጪ ለማገዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.