Fana: At a Speed of Life!

ሁሉንም አካባቢ ያማከለ ትምህርት በፍትሐዊነት ተደራሽ ማድረግ ይገባል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ እና የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በጋምቤላ ከተማ ሁለት ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታን አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ ሁሉንም አካባቢ ያማከለ ትምህርት በፍትኃዊነት ተደራሽ ማድረግ ይገባል።

ትውልዱን ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

የትምህርት ተቋማት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስቴሩ ሚናውን ይወጣል ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ የሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማስጀመር ብቻ ሳይሆን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ሚኒስቴሩ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ግንባታቸው ለተጀመሩት ሞዴል ትምህርት ቤቶች ስኬታማነት የማህበረሰቡ ተሳትፎ መጠናከር እንደሚኖርበትም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ፤ በክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ሚኒስቴሩ እያከናወነ ያለው ተግባር ጥራትንና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ አቅም የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ስኬታማነት የክልሉ መንግስትና ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኡኩኝ ኡኬሎ በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብርን በመጠቀም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን በይፋ የተጀመሩት ሁለት ሞዴል ትምህርት ቤቶች ይህንኑ ያጠናክራሉ ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.