Fana: At a Speed of Life!

ዓለም የደረሰበትን የላቀ የአንሜሽንና ፊልም ሥራ በስፋት መጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዓለም የደረሰበትን የላቀ የአንሜሽንና ፊልም ሥራ በማስፋፋት ዘመናዊ የፊልም አሠራር ሂደትን ማጠናከር ይገባል አለ፡፡

‘ኢማጂንግ አኒሜሽን ሚዲያ’ የስልጠና ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነትም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኮል ጆን ሲ ሮቢንሰን ማዕከል ጋር ተፈራርሟል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ስልጠናው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ አኒሜሽን፣ ሮቦቲክስ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሲኒማቶግራፊ፣ ዲጂታል አርት፣ የፊልምና ሚዲያ ፕሮዳክሽንን ያካተተ ነው፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎችም፤ የኢትዮጵያን መልክ፣ ታሪክና ባህል ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ እንዲገልፁ አቅማቸውን የሚያዳብሩበት ነው ብለዋል፡፡

ዓለም የደረሰበትን የላቀ የአንሜሽንና ፊልም ሥራ በማስፋፋት ዘመናዊ የፊልም አሠራር ሂደትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ስልጠናው በአሜሪካዊ የፊልም ባለሙያ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ተከፋፍሎ እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በዲጂታል ክኅሎት የላቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እና ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

በሔኖክ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.