የኢትዮጵያን ባህል እና ጥበብ የሚያስተዋውቅ የከያኒያን ቡድን ወደ ተለያዩ ሀገራት ይጓዛል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ባህል እና ጥበብ የሚያስተዋውቅ የከያኒያን ቡድን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ይጓዛል አለ።
ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ ያደረጉት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) እንደገለጹት፤ የከያኒያን ቡድኑ 70 የሚጠጉ አባላትን ይዟል።
ቡድኑ ሩሲያ እና ብራዚልን ጨምሮ በበርካታ የዓለም ሀገራት ተዘዋውሮ በሚያቀርበው የኪነ ጥበብ ሥራ የኢትዮጵያን ባህል፣ ጥበብ፣ እሴት እና ታሪክ ያስተዋውቃል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በ1978 ዓ.ም መሰል የባህል እና ጥበብ ጉዞ መደረጉን አስታውሰው፤ በጉዞው የኢትዮጵያን ገጽታ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የከያኒያን ቡድኑ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ከዛም ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎለብት እንደሆነና የባህልና ጥበብ ዲፕሎማሲን በማሳደግ ሂደት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
የባህል እና ጥበብ ጉዞው የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በማየት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚደረግ መሆኑንም ሚኒስትር ዴዔታው ተናግረዋል፡፡
በአቤል ንዋይ