በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 32 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 32 ሺህ ኩንታል የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር ለመኸር እርሻ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የግብዓት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለመኸር እርሻ ለማቅረብ ከታቀደው ምርጥ ዘር ውስጥ 26 ሺህ ኩንታል ለስርጭት ዝግጁ ሆኗል።
የአርሶአደሮችን ፍላጎት ለማሟላት ቀሪውን ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች ክልሎች በማግኘት ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን ገልጸው÷ በቀጣይ የምርጥ ዘር ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርጥ ዘር ብዜት ሥራው እንደ ሀገር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሰብሎችን ዘር የማባዛት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 2 ሺህ 46 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች ዘር በማምረት 46 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መገኘቱን አመልክተዋል።
የበቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ሩዝ እና ማሽላ ለመኸር እርሻ ለማሰራጨት የተዘጋጁ ምርጥ ዘሮች እንደሆኑም ጠቁመዋል።
በአድማሱ አራጋው