ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ ተዘጋጅቷል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማት ዴስክ ኃላፊ ሻንቆ ቴሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለመርሐ ግብሩ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ ተዘጋጅቷል።
1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ጠቁመው ÷ ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ መለየቱን ተናግረዋል።
ለተከላ ከተለየው ውስጥ ከ492 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ካርታ መዘጋጀቱን የጠቀሱት ሃላፊው ÷ በበልግ ተከላ ወቅት 518 ነጥብ 9 ሚሊየን ችግኝ መተከሉን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ለመርሐ ግብሩ እስካሁን 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ጉድጓድ መዘጋጀቱን እና ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የችግኝ ዝግጅቱ በመንግሥት ፣በግል እና በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በት/ቤቶችና በአርሶ አደሮች ጓሮ በሚገኙ ከ116 ሺህ በላይ ችግኝ ጣቢያዎች መከናወኑን አመልክተዋል።
የደን፣ የቀርከሃ፣ የጥምር ደን፣ የከተማ ውበት ችግኞችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ነው ያስረዱት፡፡
የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሻንቆ ÷ ለዚህም በየሣምንቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የስትሪንግ ኮሚቴ ግምገማ እየተካሄደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው