የሎጂስቲክስ ዘርፍ አገልግሎትን የተሳለጠ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሎጂስቲክስ ዘርፉን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀና የተሳለጠ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ።
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሚኒስቴሩ አዲስ አርማ (ሎጎ) በዛሬው ዕለት የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ አዲሱ አርማ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተግባር ከሌሎች ተቋማት ተለይቶ የሚታወቅበት ነው።
ሚኒስቴሩ አሠራሩን ለማሻሻልና ተገልጋዮችን ለማርካት በርካታ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸው÷ አዲሱ አርማ ከዛሬ በኋላ ሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል።
አርማው ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ማስፈፀሚያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አዲሱ አርማ የተቋሙን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴትን በሚገልፅ መልኩ የተዘጋጀና እየሠራ ያለውን ተግባር ያካተተ ነው ተብሏል።
በየሻምበል ምህረት