14 ሀገራት የሚሳተፉበት ‘አግሮ ፉድ’ የንግድ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 14 ሀገራት የሚሳተፉበት 7ኛው አግሮ ፉድ የንግድ ዓውደ ርዕይ ከሰኔ 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የጀርመኑ ፌርትሬድ እና ፕራና ኢቨንትስ በጋራ በሚያካሂዱት ዓውደ ርዕይ ዓለም ዓቀፍ የግብርና፣ የምግብና መጠጥ ግብዓቶች እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፕላስቲክ፣ ሕትመትና የማሸጊያ ቴክኖሎጂ እና ምርቶች ለእይታ ይቀርባሉ።
ቻይና፣ ጀርመን፣ ሕንድ፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቱርክ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ130 በላይ ድርጅቶች በዓውደ ርዕዩ ላይ በመሳተፍ ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን ያቀርባሉ።
በግብርና፣ ምግብና መጠጥ እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ በሚያስችለው በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱ ተመልክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የምግብ ንግድ ትርኢት እና ኢትዮፒካ የቡና ንግድ ትርኢት ጎን ለጎን እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
በዮናስ ጌትነት