Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና በሌሎች ጉዳዮች ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

ፕሬዚዳንቱ አዲስ የተሾሙትን የአውስትራሊያ፣ ኩባ፣ አልጄሪያ፣ ጋምቢያ፣ ጆርጂያ፣ማይናማር፣ ታይላንድ፣ ቪየትናምና ቆጵሮስ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት ከሀገራቱ አምባሳደሮች ጋር የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች የትብብር መስኮችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች መክረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ኤምባሲ የሌላቸው ሀገራት ኤምባሲ በሚከፍቱበት ሁኔታ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የኩባ አምባሳደር ሜይሊን ሱአሬዝ አልቫሬዝ ኢትዮጵያና ኩባ ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፥ ይህንን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ ትምህርትና ጤና ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ በሰጡት ማብራሪያ አንስተዋል፡፡

የጋምቢያ አምባሳደር ሳሊማታ ኢቲ ቶሬይ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ጋምቢያ ያላቸውን ጥልቅ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንደሚያከናወኑ ጠቁመዋል።

በባህል፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም ንግድ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የገለጹት የታይላንድ አምባሳደር ሞራኮት ጃንማቱኮርን በበኩላቸው፥ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ አቅሞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ የታይላንድ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በኢትዮጵያ የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር ጉብኝት እንደሚያደርጉም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

የቆጵሮስ አምባሳደር ሳቫስ ቭላድሚሮ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ የቆጵሮስ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን በማውሳት የሀገራቱን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.