በቦንጋ ከተማ በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ እየተገነባ ያለው ቤተ መጻሕፍት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ እየተገነባ ያለውን ቤተ መጻሕፍት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፡፡
ለግንባታው ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ እና ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ እንደሚሸፈን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ የማታለም ቸኮል (ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡
ግንባታው በጥራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙም ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
ለሥራው ስኬታማነት ክልሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ቤተ መጻሕፍቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአንድ ጊዜ 200 ሰዎችን ያስተናግዳል ብለዋል፡፡
ቤተመጻሕፍቱ በዲጂታልና ዘመናዊ በሆነ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝም ነው ለፋና ዲጂታል የተናገሩት፡፡
ለአገልግሎት ክፍት ሲሆንም፤ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች፣ ለተመራማሪዎችና ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጽሐፋቸው ገቢ ለትውልድ ግንባታ አስተዋጽዖ በሚያበረክተው የቤተ መጻሕፍት ግንባታ ላይ እንዲውል ላደረጉት አበርክቶም አመሥግነዋል፡፡
በአድማሱ አራጋው