Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከ28 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በቡና ልማት ተሰማሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ28 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ በላይ ባለሃብቶች በቡና ልማት ላይ ተሰማርተዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በክልሉ 1 ሺህ 468 ባለሃብቶች በቡና ልማት ዘርፍ ላይ መሰማራቱንና በዚህም ለ16 ሺህ ዜጎች ቋሚ እንዲሁም ከ69 ሺህ በላይ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን አመልክቷል።

የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድሳኒ አሚን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በቡና ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች የቡናን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ስራ እየሰሩ ነው።

ባለሃብቶቹ ምርጥ ዘር እና የቡና መልቀሚያ ኮምባይነርን ጨምሮ የቡና ልማት ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ጥራት ያለው ቡና በማምረት ለውጪ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸው ይህም የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከአካባቢው ማሕበረሰብ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሲፈን መገርሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.