Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ከተሞች ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

እንደ ሀገር የኮሪደር ልማት ሥራ በመዲናዋ ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ በመውሰድ የኮሪደር ልማት በቦንጋ እና ሚዛን ከተሞች ቀድሞ መጀመሩን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ የማታለም ቸኮል (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

በዚህም በቦንጋ ከተማ 0 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ በ22 ሚሊየን ብር ወጪ መከናወኑን አስታውሰው÷ ሁለተኛ ዙር ሥራውን በ5 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ታቅዶ በ200 ሚሊየን ብር በጀት የግንባታ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ሥራው ከመጀመሩ በፊት ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠርና በማሳተፍ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን መከናወናቸውን ገልጸው÷ ግንባታው 35 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማት አካል የሆነ የመዝናኛ ፓርክ በቦንጋ ከተማ በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መገንባቱን ጠቅሰው፥ ይህም ለሌሎች ከተሞች ሞዴል በሚሆን መልኩ መገንባቱን አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡም በከፍተኛ ተነሳሽነት የኮሪደር ልማት ሥራውን በመደገፍ 73 ሚሊየን ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሚዛን ከተማ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማት ኅብረተሰቡ ወደ 17 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ማዋጣቱን አንስተው÷ በዚህም የአንድ ኪሎ ሜትር ሥራ እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ወደ 26 ኪሎ ሜትር አካባቢ የመንገድ ፕላን ጥሰት ያለበትን የመለየት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በቴፒ፣ ታርጫ እንዲሁም በሌሎች የክልሉ ከተሞች ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ በፊት የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጥበትን ጨምሮ የወሰን ማስከበር ሥራዎች የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይከናወን ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.